#IOM

እንደ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት መረጀ በመቶዎች የሚቆጠሩ የቱርክ ዜጎችን ጨምሮ ከ3,500 በላይ ሰዎች በሱዳን ያለውን ከባድ ጦርነት ሸሽተው በመተማ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል።

ከሚያዚያ 21 እስከ 25 ባለው ጊዜ ውስጥ ከ3500 በላይ የሆኑ የ35 ሀገራት ዜጋ  ስደተኞች ተመዝግበዋል።

ከተመዘገቡት አጠቃላይ ስደተኞች መካከል ከ40 በመቶ በላይ የቱርክ ዜጎች ሲሆኑ፣ ኢትዮጵያውያን 14 በመቶ ናቸው።

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ 200 የነበረው የስደተኞቹ ቁጥር  ያለፈው ማክሰኞ ወደ 1,300 ደርሷል።

ድርጅቱ በሱዳን ድንበር ላይ ለሚደርሱ 700 ያህል የሶስተኛ ሀገር ዜጎችን ለመቀበል የትራንስፖርት እርዳታ በርካታ ኤምባሲዎች ጥያቄዎች  እንዳቀረቡለት ታውቋል።

የአይኦኤም ባለስልጣናት ከድንበር ከተማ መተማ ወደ ጎንደር እና አዲስ አበባ ከተሞች የሚመጡ ስደተኞች መብዛትን ተከትሎ  ትራንስፖርት በማዘጋጀት ላይ ናቸው።

ድርጅቱ የሱዳኑ ግጭት  270,000 የሚደርሱ ሰዎችን ወደ ጎረቤት ደቡብ ሱዳን ፣ ቻድ፣ ግብፅ እና ኢትዮጵያ እንዲሰደዱ ሊያደርግ ይችላል ብሏል።

በሱዳን ወታደሮች እና ታጣቂዎች መካከል የተደረገው ጦርነት ሚያዝያ 15 ቀን 2023 ከተቀሰቀሰ ወዲህ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲሞቱ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ለስደት ተዳርገዋል።

በርካታ የሀገሪቱ ዜጎችም በከፍተኛ የውሃ፣ የምግብ፣ የመድሃኒት እና የነዳጅ እጥረት እየተሰቃዩ ነው።

በሌላ በኩል፤ ከቀናት በፊት በተፋላሚ ወገኖች ስምምነት የተደረሰበት የ72 ሰዓታት የተኩስ አቁም ለተጨማሪ ቀናት እንዲራዘም የተደረገ ቢሆን አሁንም በሀገሪቱ ግጭት ቀጥሏል።

ተኩስ አቁሙ እንዲራዘም የተደረገው በሱዳን ጎረቤት አገራት እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት፣ በአሜሪካ እና በዩናይትድ ኪንግደም ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ነው ተብሏል።

ምንጭ፦ አጀንስ ፍራንስ ፕሬስ / ዶቼ ቨለ

@tikvahethiopia