#ባጃጅ

" በአነስተኛ ገቢ የሚተዳደሩ፣ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያንን እንዲሁም ሴቶች እና ሕፃናትን ታሳቢ በማድረግ እገዳውን ማንሳትና ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ መፈለግ ያስፈልጋል " - ዶ/ር ዳንኤል በቀለ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ የባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎትን ከየካቲት 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በከተማዋ በየትኛውም አካባቢ ላልተወሰነ ጊዜ እንዳይሰጥ እገዳ መጣሉና በተለያዩ ሰብአዊ መብቶች ላይ ተገቢ ያልሆነ ገደብ የሚጥል እርምጃ በመሆኑ እጅግ አሳሳቢ ነው ብሏል።

ኮሚሽኑ ይህንን በተመለከተ በላከልን መግለጫው እገዳውን ተከትሎ የደረሱትን አቤቱታዎች መሠረት በማድረግ የአ/አ የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊዎችን አነጋግሯል።

ኃላፊዎቹ ተከታዩን ብለዋል ፦

- በከተማዋ ወደ 10 ሺህ የሚገመቱ የባጃጅ ተሽከርካሪዎች በከተማ አስተዳደሩ የሥራ ፈቃድ ያልተሰጣቸው ናቸው።

- እንደ አንድ አገልግሎት ሰጪ በከተማዋ አሠራር ሥርዓት ያልተዘረጋላቸው መሆኑን፣ ሌሎችም ተዛማጅ ችግሮች አሉ።

- ነባራዊ ሁኔታ ከግምት በማስገባት ከዋና መንገዶች ውጪ ባሉ ውስጥ ለውስጥ መንገዶች እስከ ሁለት ኪሎ ሜትር ድረስ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ማስተካከያ እየተወሰደ ቢቆይም በአንዳንድ አካባቢዎች ባጃጆቹ ከተቀመጠላቸው የእንቅስቃሴ አካባቢ ውጪ በዋና መንገዶች ላይ ሲሠሩ በመታየታቸው እና የከተማው የትራንስፖርት ፍሰት ላይ ጫና ፈጥሯል።

- እገዳው በሁሉም ቦታ የተደረገው ልዩነት እና መድሎ ላለመፍጠር ነው፡ የባጃጅ ትራንስፖርት አሽከርካሪዎች በማኅበር ተደራጅተው የሚሠሩ በመሆኑ አሠራሩን ስለማሻሻል ከማኅበራቱ ጋር የተደረጉ ውይይቶች ነበሩ።

ኢሰመኮ ባደረገው ክትትል እገዳው በከተማዋ ሙሉ በሙሉ ተፈጻሚ በመሆኑ የባጃጅ ትራንስፖርት አሽከርካሪዎቹንና ቤተሰባቸውን ብቻ ሳይሆን፣ እጅግ በርካታ ተጠቃሚዎችንም ችግር ላይ እንደጣለ መረዳት እንደተቻለ ገልጿል።

መንግሥት ሰዎች ሥራቸውን እና የመረጡትን መተዳደሪያ ያለአግባብ እንዳያጡ ማድረግን ጨምሮ የመረጡትን እና የተቀበሉትን ሥራ እንዲሠሩ የማስቻል ኃላፊነት አለበት ያለው ኢሰመኮ በኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 41(1) መሠረት “ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሀገሪቱ ውስጥ በማንኛውም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የመሰማራት እና ለመተዳደሪያው የመረጠውን ሥራ የመሥራት መብት ” ያለው መሆኑን በንዑስ-አንቀጽ 2 እንደተመለከተው ደግሞ መተዳደሪያውን፣ ሥራውን እና ሙያውን የመምረጥ መብት አለው ማለቱን ጠቅሷል።

ይህ መተዳደሪያን የመምረጥ/በመረጡት ሥራ የመሰማራት መብት (the right to choose one’s livelihood/work) ኢትዮጵያ ባጸደቀቻቸው የተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሰነዶችም የተረጋገጠ መብት ነው ሲል ኮሚሽኑ አስገንዝቧል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ  በባጃጅ የትራንስፖርት ሥራ የተፈጠሩትን ችግሮች በተገቢው ሕጋዊ እርምጃዎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች በማስተዳደር እና ወደ ሕጋዊ አሠራር እንዲገቡ ማድረግ ሲገባ በጠቅላላ ከተማው ላልተወሰነ ጊዜ ገደብ መጣሉ ከላይ ሕገ-መንግሥታዊ ጥበቃ የተደረገላቸው መብቶችን አደጋ ላይ የጣለ እርምጃ ነው ብለውታል።

በተለይ በአነስተኛ ገቢ የሚተዳደሩ፣ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያንን እንዲሁም ሴቶች እና ሕፃናትን ታሳቢ በማድረግ እገዳውን ማንሳትና ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ መፈለግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

(ሙሉ መግለጫ ከላይ ተያይዟል)

@tikvahethiopia