TIKVAH-ETHIOPIA
Photo
#Update

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መገናኛ ብዙሃን ዛሬም እስር እና ማንገላታት ቀጥሎ መዋሉን ገለፁ።

ተሚማ የተሰኘው ሚዲያ ፤ በዛሬው ዕለት የአርሲ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ኅሩያን ታምራት ወልዴ መታሰራቸውን ገልጿል።

ሚዲያው ፤ " ሕገ ወጡን ቡድን የሚደግፉት የመንግሥት አካላት ሥራ አስኪያጁን ቁልፍ አስረክበው እንዲወጡ ቢነግሯቸውም አልቀበልም በማለታቸው ዛሬ ጠዋት ታሥረዋል " ሲል ነው ያስረዳው።

በሌላ በኩል በሀገረ ስብከቱ ያሉ 13 ወጣቶችም በዛሬው ዕለት መታሠራቸው ተነግሯል።

በሌላ በኩል በቅዱስ ሲኖዶስ ትዕዛዝ ዛሬ የኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ምዕመናን ጥቁር ለብሰው የዋሉ ሲሆን ጥቁር ልብስ የለበሱ ምእመናን በኮልፌ ፊሊዶሮ ልደታ፣ በቀራንዮ መድኃኔዓለምና በወይብላ ማኅደረ ስብሐት ቅድስት ማርያም አብያተ ክርስቲያናት አካባቢ ፖሊስ ድብደባ መፈፀሙን የቤተክርስቲያና መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

በሌላ በኩል በአንዳንድ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ሰራተኞች ጥቁር እንዳይለብሱ ፤ የቤተክርስቲያኗን ትዕዛዝ እንዳይፈፅሙ የማድረግ እንቅስቃሴ መኖሩን የቤተክርስቲያኗ መገናኛ ብዙሃን አሳውቀዋል።

ጾመ ነነዌን ምክንያት በማድረግ ምዕመናን #ጥቁር_ልብስ ብቻ በመልበስ በጾምና በጸሎት ምሕላ በመያዝ በቤተ ክርስቲያን ዓውደ ምሕረት በመገኘት ጸሎትና ምሕላ እንዲያቀርቡ በቤተክርስቲያኗ የቀረበው ጥሪ በቀጣይ ቀናትም ተግባራዊ ሆኖ ይቀጥላል።

ፎቶ፦ የጾመ ነነዌ የፀሎት ስነስርዓት

@tikvahethiopia