#ETHIOPIA #USA

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊነከን ጋር በስልክ መወያየታቸውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤት አሳውቋል።

ውይይታቸው ትኩረቱን ያደረገው የሰላም ስምምነቱን አፈፃፀም በተመለከተ እንደነበር ተመላክቷል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መ/ቤት ይፋ ባደረገው መረጃ፤ የኤርትራ ወታደሮች ከሰሜን ኢትዮጵያ እየወጡ መሆኑን በማመልከት በዚህም ጉዳይ ብሊንከን ከጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ መነጋገራቸውን ገልጿል።

ብሊንከን ፤ የታየውን መሻሻል (የኤርትራ ሰራዊት መውጣት መጀመር) በደስታ መቀበላቸው፤ ይህም በሰሜን ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ቁልፍ መሆኑን የገለፁ ሲሆን የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ተቆጣጣሪዎች ወደየአካባቢዎቹ እንዲደርሱ አሳስበዋል።

ብሊንከን ፤ ሀገራቸው አሜሪካ በአፍሪካ ህብረት መሪነት እየተካሄደ ላለው የሰላም ሂደት ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል ለዶ/ር ዐቢይ አህመድ አረጋግጠዋል።

በተጨማሪ፤ ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ እና ብሊንከን በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ያለውን አለመረጋጋት እንዲያበቃ በማድረግ አስፈላጊነት ላይም መመካከራቸው ተገልጿል።

ይህንን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት መረጃ በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግሥት ኮሚኒኬሽን /ከጠ/ሚ ፅ/ቤት/ ከራሳቸው ከጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ በኩል ምንም የተባለ ነገር የለም።

የኤርትራ ወታደሮችን ከሰሜን ኢትዮጵያ በተለይ ከትግራይ ክልል መውጣትን በተመለከተ ከሰሞኑን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ነዋሪዎችን ዋቢ አድርገው ዘገባ እያቀረቡ ይገኛሉ ነገር ግን  ወታደሮቹ እየወጡ ስለመሆኑ ከአፍሪካ ህብረት/ ከኢትዮጵያ መንግሥት/ከትግራይ ክልል አመራሮች በኩል እስካሁን ምንም ይፋዊ መግለጫ አልተሰጠም።

@tikvahethiopia