#Eritrea

ባለፉት ሁለት ቀናት ከጎረቤት ኤርትራ ሠራዊት ጋር አዲስ ውጊያ መካሄዱን የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ገልፀዋል።

አቶ ጌታቸው ዛሬ ግንቦት 22/2014 ዓ.ም አመሻሽ ላይ እንዳሉት ባለፈው ቅዳሜ እና እሑድ (ግንቦት 20 እና 21 ቀን 2014 ዓ. ም.) የኤርትራ ሠራዊት በሽራሮ ጥቃት ከፍቶ ነበር ብለዋል።

በውጊያው አንድ የኤርትራ ጦር ብርጌድ አዛዥ እና 3 የሻለቃ አዛዦች የሚገኙባቸው 120 ወታደሮችን እንደተገደሉ 195 ያህሉን እንዳቆሰሉ እና 4 ወታደሮችን እንደተማረኩ ተገልጿል። አንድ ድሽቃ፣ አምስት የወታደራዊ ሬዲዮ መገናኛዎች እና በርካታ የጦር መሳሪያዎች ከኤርትራ ጦር እንደተማረከም ተገልጿል።

ቅዳሜና እሁድ ተከሰተ ካሉት ወታደራዊ ግጭት በተጨማሪ ከ4 ቀናት በፊት ግንቦት 16 ቀን 2014 ዓ. ም. የኤርትራ 57ኛ እና 21ኛ ክፍለ ጦር ወደ ትግራይ ክልል ጥቃት ሰንዝሮ እንደነበርና አዲአዋላ በተባለው አካባቢ ይህንን ጥቃት መመከት እንደተቻለ አሳውቀዋል።

አቶ ጌታቸው ዓለማቀፉ ኅብረተሰብ የኤርትራን መንግሥት ድርጊት በቃ እንዲለው ጥሪ አቅርበዋል።

ይህን ጉዳይ በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይ ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ለቢቢሲ በሰጡት ቃል ተካሄደ ስለተባለው ውጊያ መረጃው እንደሌላቸው ገልጸው፣ ነገር ግን የኤርትራ ኃይሎች ጥቃት ሊፈጽሙ የሚችሉበት ሁኔታ የለም ብለዋል።

ዶ/ር ለገሰ " ህወሓቶች ራሳቸው ትንኮሳ ፈጽመው " የሚያሰሙት ክስ ሊሆን ይችላል ሲሉ ገልፀዋል። በአሁኑ ጊዜ " በኤርትራ በኩል ጦርነት ይከፈታል የሚል እምነት የለንም " ያሉት ዶ/ር ለገሰ የተከሰተ ነገር ካለም አጣርተው መረጃ እንደሚሰጡ መግለፃቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

በኤርትራ መንግስት በኩል እስካሁን የተባለ ነገር የለም።

@tikvahethiopia