ግብፅ እና ሱዳን ስለ ዓባይ ኃይል ማመንጨት ምን አሉ ?

በዓባይ ወንዝ ላይ የተገነባውን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት መጀመርን ተከትሎ ግብፅ እና ሱዳን ተቃውሞ አሰምተዋል።

የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪ እንዳሉት የኢትዮጵያ አካሄድ ግብጽ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2015 በካርቱም ያደረጉትን የመርህ ስምምነት የሚጥስ ነው ብለዋል።

በሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የህዳሴ ግድብ ተወካይ አምባሳደር ኦማር አልፋሩቅ ግድቡ ሀይል ማመንጨቱ 3ቱ ሀገራት የተናጥል እርምጃ እንዳይወስዱ በሚል የፈረሙትን የካርቱም ስምምነትን የሚጥስ እና ወዳጅነታቸውን የሚጎዳ ነው ሲሉ መናገራቸውን አል ዓይን ኒውስ ዘግቧል።

ጠ/ሚር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ዛሬ በግድቡ ኃይል ማመንጨት ጅማሮ ማብሰሪያ ስነስርዓት ላይ " የግድቡ ሀይል ማመንጨት መጀመር ለአህጉራችን እንዲሁም አብረናቸው ሰርተን በጋራ ለመጠቀም ለምንሻ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የምሥራች ነው። ዐባይ ወንዛችንን ሀገራችንን አልምቶ ጎረቤቶቻችንን ሊያረሰርስ ጉዞውን ቀጥሏል " ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤ " የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ወንድም የሱዳን እና የግብጽ ህዝቦች ዛሬ የተጀመረው ኃይል የማመንጨት ስራ ለእናንተም በረከት ነው እና እንኳን ደስ አላችሁ ! " ሲሉም ተናግረዋል።

" ባልተገባ ሁኔታም ቢሆን ለፈጠራችሁት ተጽእኖ እና ፈተናም ለመሰግናችሁ እወዳለሁ ፤ መላው የዓለም ህዝብ እንዲገነዘብ የምፈልገው፤ ይህ ውሃ እንደምታዩት ኃይል እያመነጨ ወደ ሱዳን እና ግብጽ የሚሄደ እንጂ ፤ ሲነገር እንደነበረው ኢትዮጵያ ውሃውን ገድባ ወንድም የግብጽ እና የሱዳን ህዝብን የማስራብ እና የመስጠማት ፍላጎት እንደሌላት በተግባር ያሳየንበት ነው፤ ለዚህም ደስ ብሎናል " ሲሉ ነው ዶ/ር ዐቢይ የተደመጡት።

@tikvahethiopia