" ... ህወሓት በከፍተኛ ደረጃ ሀይል እያሰባሰበና ሊወጋ እየተዘጋጀ መሆኑን የሚያሳዩ እንቅስቃሴዎች እያደረገ ነው " - አቶ ግዛቸው ሙሉነህ

የአማራ ክልል መንግስት ህወሓትን ማጥፋት ካልተቻለ የኢትዮጵያ ስጋት ሆኖ መቀጠሉ አይቀሬ ነው አለ።

የክልሉ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ግዛቸው ሙሉነህ ለአሀዱ ቴሌቪዥን በሰጡት ቃል " አሸባሪውን የሕወሓት ቡድን ተባብሮ ሙሉ በሙሉ ማጥፋት ካልተቻለ የኢትዮጵያ ስጋት መሆኑን ይቀጥላል " ብለዋል።

ቡድኑ አሁንም በአማራ ክልል የተለያዩ ስፍራዎች ላይ በየቀኑ ጥቃቶችን እየሰነዘረ ንፁሃንን እያሰቃየና እየገደለ ነው ሲሉም አቶ ግዛቸው ከሰዋል።

አክለው ፥ "በማይፀብሪ ፣ አዳርቃይ ፣ ቆቦ ፣ኮረም ፣አላማጣ በየቀኑ ጥቃት የሚሰነዝርባቸው እና ከጦርነት አርፈው የማያውቁ አካባቢዎች ናቸው። ቡድኑ በእነዚህ አካባቢዎች አሁንም ፍላጎት እንዳለው ያሳያል " ብለዋል፡፡

ዳይሬክተሩ ፤ ህወሓት በከፍተኛ ደረጃ ሀይል እያሰባሰበና ሊወጋ እየተዘጋጀ መሆኑን የሚያሳዩ እንቅስቃሴዎች እያደረገ እንደሆነም አመልክተዋል። አሁንም ልክ እንደ በፊቱ በሀሰት ትርክቱ እያሳመነ እንዲሁም እያስገደደ የትግራይ ህዝብን እያሰለጠነ እና እያዘመተ ነው ብለዋል፡፡

አሁን ባለዉ ሁኔታም ወረራ ለመፈፀም የተለያዩ ሙከራዎችን ቢያደርግም እንዳልተሳካለት እና ለሌላ ጥቃት እየተዘጋጀ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

ይህ ኃይል እስካልከሰመ ድርስ አርፎ የሚተኛ አይደለም ያሉት ዳይሬክተሩ እሰካሁንም ሽንፈቱን አምኖ ያልተቀመጠ እና ከስህተቱ የማይታረም መሆኑን እያሳየ ነዉ ብለዋል ለቴሌቪዥን ጣቢያው።

ምንጭ፦ አሀዱ ቴሌቪዥን

@tikvahethiopia