#Ethiopia #Kenya #Egypt

ከቀናት በፊት እዚህ ኢትዮጵያ የነበሩት የአሜሪካው ባለስልጣን ኬንያ ሄደው ከፕሬዜዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር ተወያይተዋል።

የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ዴቪድ ሳተርፊልድ ከኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር በናይሮቢ ባደረጉት ውይይት ሁለቱም አካላት በኢትዮጵያ የሚታየዉ ጦርነት እንዲያበቃ ጥረታቸዉን እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።

ሳተርፊልድ ፤ ፕሬዝዳንት ኬንያታ በኢትዮጵያ መንግስት እና በTPLF መካከል ያለውን ግጭት ለማስቆም ላደረጉት ቁርጠኝነት አመስግነዋል።

ሳተርፊልድ ለኬንያዉ ፕሬዚዳንት "የእርስዎ ሚና (የኢትዮጵያን ግጭት ለማስቆም በመርዳት) በጣም ጠቃሚ እንደነበረ እናምናለን። ኬንያ በአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ እየተጫወተች ያለውን ሚናም እናደንቃለን። በኢትዮጵያ የእናንተን እርዳታ እና ድጋፍ እንጠይቃለን። በዚያች አገር የሰራችሁት ሥራ እንዲባክን አንፈልግም" ብለዋቸል።

ኬንያታ በበኩላቸዉ ኬንያና ኢትዮጵያ ጥሩ አጋር መሆናቸውን ጠቁመው በሀገሪቱ ያለው የውስጥ ግጭት የተፈጠረውን እድገት የሚሸረሽር በመሆኑ እንዲቀጥል መፍቀድ እንደሌለበት ጠቁመዋል።

"ጠንካራና የተረጋጋች ኢትዮጵያ ለኛ ጠቃሚና አስፈላጊ ነች። ለዚህም ነው ግጭቱ እልባት እንዲያገኝ የምንችለውን ሁሉ ለማድረግ ቁርጠኛ አቋም የያዝነው" ብለዋል።

ከኢትዮጵያ ግጭት በተጨማሪ ፕሬዝዳንት ኬንያታ እና ሳተርፊልድ በሱዳንና በሶማሊያ ስላለው የሰላምና የፀጥታ ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል።

በሌላ መረጃ፦ ዴቪድ ሳተርፊልድ ዛሬ ግብፅ የገቡ ሲሆን የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪ እንደተቀበሏቸው የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳውቋል። በምን ጉዳይ እንደተወያዩ የተገለፀ ነገር የለም።

ምንጭ፦ የኬንያ ፕሬዜዳንት ፅ/ቤት (ዶቼ ቨለ) እና የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

@tikvahethiopia