#Balderas

የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት በቅርቡ ከእስር የተፈቱት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በአፋር እና አማራ ክልል የሚያደርጉትን ጉዞ ዛሬ ጥር 6 ቀን 2014 ዓ/ም ጀመሩ።

በፓርቲው ፕሬዜዳንት አቶ እስክንድር ነጋ የሚመራው የአመራሮች ቡድን ዛሬ ወደ አፋር ክልል ገብተዋል።

ቡድኑ በአፋር የዛሬ ውሎው ከሰመራ 10 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በሚገኘው ዱቢቲ ሪፈራል ሆስፒታል በማቅናት በግንባር የተጎዱ የጦር አባላትን ጠይቋል።

ባልደራስ ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ እስክንድር ነጋ የጦር አባላቱ በግንባር ለከፈሉት የህይዎት እና የአካል መስዕዋትነት የተሰማቸውን ታላቅ ክብር በራሳቸውና በድርጅቱ ስም ገልፀው ዕውቅናም እንደሚሰጡት ተናግረዋል።

በአፋር ዱቢቲ ሪፈራል ሆስፒታል በጦርነቱ ሳቢያ የተጎዱ የመከላከያ ሰራዊት አባላት፣የአፋር ልዩ ኃይል፣ የአፋር ህዝባዊ ሰራዊት እና ሚሊሻ እንዲሁም ቁስለኛ የህወሓት ሰራዊት አባላት እንደሚገኙ ተገልጿል።

አመራሮቹ ከሆስፓታል መልስ በክልሉ መስተዳድር ጥያቄ መሠረት በአፋር ዱፍቲ በአዋሽ ወንዝ እየለማ ያለውን የስንዴ ምርት መጎብኘታቸውን ፓርቲው አሳውቋል።

የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አመራሮች በአፋር ጉብኝታቸውን ሲያጠናቅቁ ወደ አማራ ክልል እንደሚያመሩ ይጠበቃል።

ፎቶ ፦ ባልደራስ ፓርቲ

@tikvahethiopia