#WFP

በትላንትናው ዕለት የተመድ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪች በትላንትናው ዕለት መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸው ላይ የዓለም ምግብ ፕሮግራም በደሴ እና በኮምቦልቻ ከተሞች የነበሩት መጋዘኖቹ በህወሓት ኃይሎች በመዘረፋቸው የምግብ እርዳታ ማቋረጡን አስታውቋል።

ቃል አቀባዩ ፥ የእርዳታ ምግብ ተከማችተውባቸው የነበሩት መጋዘኖቹ በህወሓት ኃይል በተዘረፉበት ወቅት በስፍራው በነበሩ ሠራተኞቹ መሳሪያ ተደግኖባቸው እንደነበረ አመልክተዋል።

በመጋዘኖቹ ላይ በህወሓት በተፈጸመው ዝርፊያ በምግብ እጥረት ለተጎዱ ህጻናት የሚቀርቡ አልሚ ምግቦችን ጨምሮ ከፍተኛ መጠን ያለው የምግብ አቅርቦት ክምችት ከሁለቱ ከተሞች ተወስደውበታል።

በስፍራዎቹ የነበሩ ሠራተኞቹም በጦር መሳሪያ ጭምር ጫናና ማስፈራሪያ ስለተደረሰባቸው ይህንን ዝርፊያ ለመከላከል ሳይችሉ መቅረታቸው ተገልጿል።

ይህ ዝርፊያ በአሁኑ ወቅት ከ9 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በምግብ እርዳታ ላይ ጥገኛ በሆነበት በሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የምግብ ዋስትና ችግርና የተመጣጠነ ምግብ እጦትን የበለጠ እንደሚያባብሰው ድርጅቱ ተናግሯል።

በሌላ በኩል በአማራ ክልል ለሰብአዊ አገልግሎት የሚውሉ ሶስት የWFP መኪኖች በዚህ ሳምንት በወታደሮች ታዝዘው ለራሳቸው ዓላማ መዋላቸውን ዱጃሪች ተናግረው ድርጊቱን አውግዘዋል ሁሉም አካላት የሰብአዊ እርዳታ ሰጪዎችን እንዲያከብሩና እንዲጠብቁ ጠይቀዋል።

ለአንድ ወር ያህል በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ስር የቆዩት የደሴና የኮምቦልቻ ከተሞች በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በተመራው የኢትዮጵያ ጥምር የፀጥታ ኃይሎች በዚህ ሳምንት ነፃ መውጣታቸው ይታወቃል።

@tikvahethiopia