#Dessise : ከደሴ ከተማ ውጭ ካለ ስፍራ ወደ ደሴ ከተማ በተተኮሱ የመድፍ አረሮች ምክንያት 1 ሰው ሲገደል 3 ሰዎች መቁሰላቸውን የደሴ ከንቲባ አቶ አበበ ገብረመስቀል አስታውቁ።

አቶ አበበ ገብረ ይህን ያሳወቁት ለቢቢሲ በሰጡት ቃል ነው።

ከንቲባው ጥቃቱ ትናንት ሐሙስ ጥቅምት 18/2014 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ በግምት 9:30 የተፈፀመ መሆኑን ገልፀው ፥ "የህወሓት ኃይሎች ሰላማዊ ሰዎች በሚገኙባቸው አካባቢዎች ላይ በመድፍ በፈጸሙት ጥቃት የሞትና የመቁሰል አደጋ ደርሷል" ብለዋል።

አቶ አበበ ህወሓት ትላንት 5 የመድፍ አረሮችን በከተማዋ ላይ መተኮሱን ፤ ሁለቱ መናፈሻ በሚባለው የከተማዋ አካባቢ፣ ሁለቱ ዳውዶ በሚባለው ስፋራ እንዲሁም ቀሪው አንድ ደግሞ እርሻ ሰብል ከሚባለው ቦታ ላይ መውደቁን ጠቁመዋል።

በሰዎች ላይ ሞትና የመቁሰል ጉዳት የደረሰው እርሻ ሰብል እና መናፈሻ በተባሉት ሁለት ስፍራዎች ላይ ሲሆን "በአንደኛው ቦታ 3 ንፁሃን ዜጎች ላይ ጉዳት ሲደርስ ከእነዚህ መካከል አንዱ ወዲያውኑ ህይወቱ ማለፉን" ከንቲባው ገልጸዋል።

የመድፍ ጥቃቱ ከተፈጸመባቸው ቦታዎች መካከል አንዱ በጦርነቱ ምክንያት ከሰሜን ወሎ ዞን የተፈናቀሉ ሰዎች የተጠለሉበትና እርዳታ የሚያገኙበት ስፍራ ይገኛል።

ባለፉት ጥቂት ቀናት በደሴ ከተማ አቅራቢያ በሚገኙ ስፍራዎች ውጊያ እየተካሄደ ሲሆን እየተካሄደ ስላለው ውጊያ የተረጋገጠ መረጃ ማግኘት አዳጋች ሆኗል።

የደሴ ከንቲባ አቶ አበበ ገብረ መስቀል በተለያዩ የወሎ ግንባሮች ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን አረጋግጠው፤ የከተማው ነዋሪ ግን መደበኛ ሕይወት መቀጠሉን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

@tikvahethiopia