#ደብረብርሃን

በደብረ ብርሃን ከተማ ከ1 ሺህ 500 በላይ ግለሰቦች በሕገ-ወጥ መንገድ በቤት ማኅበር ተደራጅተው እንደተገኙ የከተማው አስተዳደር አስታወቀ።

በደብረ ብርሃን ከተማ በተለምዶ 633ቱ የቤት ኅብረት ስራ ማኅበራት በሚል ከተደራጁና ዕውቅና ከተሰጣቸው ማህበራት ውስጥ ከ1 ሺህ 500 በላይ ግለሰቦች በህገወጥ መንገድ ተደራጅተው ተገኝተዋል።

ይህን የተገለፀው የደብረ ብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ም/ ከንቲባ አቶ ደስታ አንዳርጌ ከከተማና ከቀበሌ አመራሮች ጋር በማኅበራቱ አደረጃጀት ዙሪያ ውይይት ባካሄዱበት ወቅት ነው።

633ቱ ማህበራት ሲደራጁ 73 የተለያዩ ቦታዎቸ ክፍት የነበሩ ቢሆንም በ65ቱ ክፍት ቦታዎች 1 ሺህ 408 ሰዎች በህገወጥ መንገድ በመደራጀታቸው የከተማው ከንቲባ ኮሚቴ ማህበራቱ ሙሉ በሙሉ እዲሰረዙ መወሰኑ ተገልጿል።

በቀሪ 560 ማህበራት ውስጥ 110 ግለሰቦች በህገወጥ መንገድ ተደራጅተው ተገኝተዋል ያሉት ከንቲባው እነዚህ ግለሰቦች ማሕበራቱ ሳይፈርሱ ግለሰቦችን ብቻ እንዲወጡ መወሰኑን አስረድተዋል።

አሁንም መረጃ የማጣራት ስራው ቀጣይነት እዳለው የገለፁት ከንቲባው በዚህ ህገወጥ ድርጊት ውስጥ የተሳተፉ አካላትን በህግ ለመጠየቅ ይሰራል ብለዋል።

በውይይቱ ላይ በማኅበራት ከተደራጁ ግለሰቦች መካከል ፦
- በከተማዋ የማይኖሩ ፣
- መሸኛ ያላመጡ ፣
- ሐሰተኛ የጋብቻ ፍቺ የፈጸሙ ፣
- ሐሰተኛ መሸኛ ያመጡ እና ባልተሟላ መረጃ የተደራጁ መኖራቸው ተመልክቷል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በዚህ ህገ-ወጥ ድርጊት የተሳተፉ አካላት ፖለቲካዊ ፣ አስተዳደራዊ እና ህጋዊ ርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚገባ አስተያየት ሰጥተዋል።

መረጃው ከደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር የተገኘ ነው።

@tikvahethiopia