እነ አቶ ጃዋር መሐመድ ችሎት ሳይቀርቡ ቀሩ።

እነ አቶ ጃዋር መሐመድ ዛሬ ለነበራቸው ቀጠሮ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሰረት ጉዳያቸውን ለመከታተል ችሎት ሳይቀርቡ ቀርተዋል።

ጉዳያቸውን የሚመለከተው ፍርድ ቤት እንዳለው "ለተከሳሾች እና ለሰፊው ማኅበረሰብ ደኅንነት ሲባል ተከሳሾች ችሎት ፊት መቅረብ አይችሉም" ሲል ትዕዛዝ ሰጥቷል።

በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ የክስ መዝገብ ሥር የተዘረዘሩ ተከሳሾች ዛሬ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ቀጠሮ ነበራቸው።

የእነ አቶ ጃዋር መሐመድን ጉዳይ እየተመለከቱ ያሉት ዳኞች ባለፉት ጥቂት ቀናት ከፍተኛ የሆነ የምርጫ ቅስቀሳ ሲካሄድ መቆየቱን አስታውሰዋል።

"ለተከሳሾች ከፍተኛ ጥበቃ ነው የሚያስፈልገው" በማለት በምርጫ ወቅት ተከሳሾችን ወደ ችሎት ማምጣቱ አስቸጋሪ ነው ብለዋል።

በዚህም ፍርድ ቤቱ አቶ ጃዋር መሐመድን ጨምሮ 24ቱ ተከሳሾች ከምርጫው በኋላ ፍርድ ቤት ይቅረቡ ሲል ወስኗል።

ዐቃቤ ሕግ ችሎቱ በዝግ ይከናወን እንዲሁም ምስክሮቼ ከመጋረጃ ጀርባ ቃላቸውን ይስጡ በሚል አሻሽሎ ባቀረበው አቤቱታ ላይ ተከሳሾች ምላሽ እንዲሰጡ ነበር የዛሬው በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ችሎት 1ኛ የጸረ-ሸብር እና ሕገ-መንግሥታዊ ጉዳዮች ችሎት ቀጠሮ ተይዞ የነበረው።

ምንም እንኳ በችሎቱ ተከሳሾቹ ባይገኙም ሦስት የተከሳሽ ጠበቆች ተገኝተዋል።

ጠበቆቹም ዐቃቤ ሕግ አሻሽሎ ላቀረበው አቤቱታ "ያዘጋጀነው ምላሽ በተከሳሾች እጅ ስለሚገኝ የምንሰጠው ምላሽ የለም" ብለዋል። ምላሻቸውን በቀጣዩ ቀጠሮ ይዘው እንደሚቀርቡ አስረድተዋል።

ፍርድ ቤቱም በአቶ ጃዋር መዝገብ ሥር የተከሰሱ ተከሳሾችን ጉዳይ ለመመልከት ለሰኔ 21/2013 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

መረጃው የቢቢሲ አማርኛው አገልግሎት ነው።

ፎቶ : ዘአፍሪካ ሪፖርት
@tikvahethiopia