#NewsAlert በሀዋሳ ከተማና አካባቢው ትናንት ተከስቶ የነበረውን የጸጥታ ችግር ለማረጋጋት እየተሰራ መሆኑን የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ። የክለሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ቴዎድሮስ ወልደሚካኤል ለፋና ብሮድካስት እንደተናገሩት፥ በግጭቱ በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን ዛሬ ላይ ከተማዋ አንጻራዊ ሰላም ይታይባታል ብለዋል።

ግጭቱ ትናንት በታቦር ክፍለ ከተማ መንገድ በመዝጋት መጀመሩን የገለጹት ኮሚሽነሩ በድርጊቱ የተሳተፉ አካላትን በቁጥጥር ስር የማዋል ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል። እንዲሁም በግጭቱ የደረሰው የጉዳት መጠን እየተጣራ መሆኑን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል። የፀጥታ ችግሩ ከተማዋን መነሻ አድርጎ ወደ ሲዳማ ዞን ወረዳዎች መዛመቱን ያነሱት ኮሚሽነሩ፥ መንገዶች በመዘጋታቸው የጸጥታው ሀይል በፍጥነት መድረስ አለመቻሉን አስታውሰዋል። በዛሬው እለት አካባቢዎቹን የጸጥታ አካላት #እያረጋጉ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ማንኛውም ጥያቄ ያለው አካል የህግ የበላይነትን ባከበረ መልኩ ማቅረብ እንደሚኖርበት ጠቅሰው፥ በክልሉ ሌሎች አካባቢዎች #ሰላም መሆኑን አስረድተዋል። ነገር ግን ከዚህ ውጭ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የዜጎችን ህልውና የሚፈታተኑ በመሆኑ ሊቆም ይገባል ነው ያሉት፡፡ ህብረተሰቡም የሀዋሳ ከተማና አካባቢውን ሰላም እና መረጋጋት ለማስጠበቅ ከጸጥታ ሀይሉ ጋር በቅንጅት እንዲሰራና አካባቢውን እንዲጠብቅ ጠይቀዋል።

ምንጭ፦ ፋና ብሮድካስቲንግ
@tsegabwolde @tikvahethiopia