አፋን ኦሮሞ በሃያ ትምህርት ቤት ሊሰጥ ነው...

በቀጣዩ ዓመት አፋን ኦሮሞ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በሃያ ትምህርት ቤት ለመስጠት መታቀዱን በኦሮሚያ ክልል በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ተናገሩ፡፡

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ቁጥሩ በርካታ የሆነ የኦሮሞ ህዝብ እንደሚኖር የተናገሩት ዶክተር ግርማ፣ በዚህ ዓመት በሃያ ትምህርት ቤት ይሰጣል ተብሎ የታሰበ ቢሆንም፤ ከሰላም መደፍረስ የተነሳ አስር ትምህርት ቤት ብቻ እንዲወሰን መደረጉን ገልፀዋል፡፡ ይሁንና ይህን ቁጥር በቀጣዩ ዓመት ከፍ በማድረግ ወደሃያ ለማድረስ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡

በኦሮሚያና ቤኒሽንጉል ጉምዝ አማካይነት የማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ እንዲቋቋም በመደረጉ በኦሮሚያ በኩል የረጅም ጊዜ ጥያቄ የነበረው በአፋን ኦሮሞ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ትምህርት እንዲሰጥ ማድረግ ያስቻለ በመሆኑ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አመልክተዋል፡፡

በዚህ ዓመት በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በአስር ትምህርት ቤት በአፋን ኦሮሞ ትምህርት እንዲሰጥ መደረጉ እንደ ትልቅ ስኬት እንደሆነም ዶክተሩ አልሸሸጉም፡፡ ባለፈው በሁለቱ ክልልች የተደረገው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ወቅት በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጋር በመሆን ተዘዋውረው ትምህርት ቤቶቹን ማየታቸውን የገለፁት ዶከተር ግርማ፣ የረጅም ጊዜ የነበረው ጥያቄ ተመልሶ ማየት መቻላቸውን ጠቅሰው፤ ትምህርት ቤቱን ያዘጋጁት የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መሆኑን ተናግረው፤ የኦሮሚያ ክልል ደግሞ መምህራኑን ወስዶና አሰልጥኖ እንዲያስተምሩ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል፡፡

Via #EPA
@tsegabwolde @tikvahethiopia