ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ👆

ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በተፈጠረ ግጭት አንድ ተማሪ መሞቱን ተማሪዎች ለቢቢሲ ገለጹ። ሟች ሰዓረ አብርሃ እንደሚባልና የሶስተኛ ዓመት የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ተማሪ እንደነበረ ለማወቅ ተችሏል።

በዩኒቨርስቲው ከዓርብ ጀምሮ የተቀሰቀሰው ግጭት እስከዛሬ ድረስ #አለመረጋጋቱን ተማሪዎቹ ገልጸዋል።

በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የህዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ደሳለው ጌትነትም በተቋሙ ከባለፈው አርብ 11 ሰዓት ጀምሮ ግጭቶች መኖራቸውን #አረጋግጠዋል።

በዚህም አርብ ግንቦት 16 ላይ 3 ልጆች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተናግረው ልጆቹ አሁን ሆስፒታል ይገኛሉ ብለዋል። የተጎዱት ተማሪዎች በባህርዳር እና አዲስ አበባ ሪፈራል ተጽፎላቸው ወደዚያው መወሰዳቸውንም ጨምረው ያስረዳሉ።

በግጭቱ ሁለት ተማሪዎች በድንጋይና በዱላ ጉዳት እንደደረሰባቸው የዓይን እማኞቹ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

በተፈጸመበት ጥቃት ምክንያት አንደኛው ተማሪ ወድያውኑ ህይወቱ ማለፉንና ሌላኛው ተማሪ ደግሞ ለህክምና እርዳታ ወደ ባህርዳር መወሰዱን ከተማሪዎቹ መረዳት ተችሏል።

የረብሻውን ምክንያት እስካሁን ማረጋገጥ አልቻልንም ያሉት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አርብ ዕለት ተሳትፎ የነበራቸውን የተወሰኑ ልጆች ፖሊስ ተከታትሎ ከግቢ ውጭ ይዟቸው ፖሊስ ጣቢያ ስለሚገኙ ጉዳያቸው እየተጣራ ነው በማለት የግጭቱ መንስኤ ከዚያ በኋላ ተጣርቶ የሚታወቅ ይሆናል ብለዋል።

በአሁኑ ሰዓት በዩኒቨርሲቲው አዳራሽ የተጠለሉ ተማሪዎች እንዳሉ የተገለፀ ሲሆን ትላንት የሟችን አስክሬን ለመሸኘት የተሰበሰቡ ተማሪዎችም "ትምህርቱ ይቅርብን ወደ መጣንበት መልሱን" በማለት ለዩኒቨርሲቱው ፕሬዚዳንት ጥያቄ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።

የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንቱ በበኩላቸው በፖሊስና የፌደራል ጸጥታ ሃይሎች እገዛ ደህንነታችሁ ለማስጠበቅ እንሰራለን በማለት ምላሽ መስጠታቸውን ተማሪዎቹ ይናገራሉ።

አሁን ረብሻ የለም፤ ተማሪዎች ግን ወደ ትምህርትም ሆነ ወደ ጥናት የሚያመሩበት ሁኔታ የለም። ችግሩ ስለማይታወቅ ከፖሊስ ጋር ችግሩን በመለየትና መፍትሔ ለመስጠት እየሠራን ነው ያሉት ደግሞ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ናቸው።

ግጭቱ በብሔር መካከል የተነሳ አይደለም የሚሉት ኃላፊው ትምህርት አለመጀመሩን አረጋግጠው የመማር ማስተማሩ ስራ ግን ማክሰኞ ይቀጥላል ብለዋል።

ለምርመራ ወደ አዲስ አበባ የተላከው የሟች ተማሪ አስከሬን ዛሬ ከሰአት ወደ ትውልድ ስፍራው ትግራይ ሽረ እንዳስላሴ ከተማ እንደሚላክ አንድ ስሟ እንዲገለጽ ያልፈለገች ተማሪ ለቢቢሲ ተናገራለች። አቶ ደሳለው በበኩላቸው አስከሬኑ ለምርመራ ወደ አዲስ አበባ እንዳልተላከና ወደ ቤተሰቦቹ እንደተሰኘ ገልፀዋል።

Via #BBC
@tsegabwolde @tikvahethiopia