የታሪፍ ማሻሻያ ተደረገ‼️

የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ በአዲስ-አዳማ የክፍያ መንገድ ታሪፍ ላይ #ማሻሻያ ማድረጉን አስታወቀ።

ኢንተርፕራይዙ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው የተሻሻለው ታሪፍ ከየካቲት 22 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል።

ማስተካከያው በክፍያ ጣቢያና በተሽከርካሪ አይነት የተደረገ ሲሆን ከ2 እስከ 16 ኪሎ ሜትር ለተሽከርካሪ 1 እና 2 የተደረገው የዋጋ ተመን 15 ብር ነው።

ከ2 እስከ 64 ኪሎ ሜትር ከተሽከርካሪ 5 እስከ 7 የተደረገው የዋጋ ተመን 80 ብር ሆኗል።

ሌሎች የዋጋ ጭማሪዎችን በኢንተርፕራይዙ ድረገጽ www.etre.com.et መመልከት ይቻላል።

ኢንተርፕራይዙ አብዛኛው ለጥገና የሚውል ጥሬ ዕቃ በአገር ውስጥ ስለማይገኝና ከወቅቱ የውጭ ምንዛሬ ዋጋ አንጻር የውጭ ብድርን በብቃት ለመክፈል የታሪፍ ማሻሻያ ማድረግ ማስፈለጉን አስታውቋል።

ወቅታዊ የገበያ ዋጋ ግሽበት የሚያስከትለውን ጫና ለመቋቋምና በአገልግሎት አሰጣጥ የተገኙ ልምዶችን በመውሰድ አሳማኝና መጠነኛ የታሪፍ ማሻሻያ ተደርጓል ነው ያለው።

የመንገዱ ተጠቃሚዎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግና የተደረገውን የታሪፍ ለውጥ አውቀው ተግባራዊ እንዲያደርጉ ኢንተርፕራይዙ አሳስቧል።

ኢንተርፕራይዙ ለጥገናና ለውጭ እዳ ክፍያ በየዓመቱ የታሪፍ ማሻሻያ እንደሚያደርግ ቢያስታውቅም ለ4 ዓመታት በነበረው ታሪፍ ሲሰራ ቆይቷል።

በተያዘው በጀት ዓመት በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሰረት የክፍያ ታሪፍ ማሻሻያ አጥንቶ ተግባራዊ አድርጓል።

የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ የመንግስት የልማት ድርጅት ሲሆን የአዲስ አዳማን የፍጥነት መንገድ የማስተዳደር፣ በክፍያ የመንገድ አገልግሎት የመስጠት፣ መንገዱን የማስጠገንና ሌሎች ተጓዳኝ ስራዎች ሃላፊነት ተሰጥቶታል።

ምንጭ፦ ኢዜአ
@tsegabwolde @tikvahethiopia