አቶ ኢሳያስ ከእስር #እንዲፈቱ ትዕዛዝ ተሰጠ‼️

የሥር ፍርድ ቤት ማለትም የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አሥረኛ ወንጀል ችሎት በ100 ሺሕ ብር ዋስ እንዲፈቱ ትዕዛዝ ከሰጠ በኋላ፣ ትዕዛዙ በይግባኝ ታግዶ ለአንድ ወር ታስረው የከረሙት አቶ #ኢሳያስ_ዳኘው በተመሳሳይ ዋስትና ከእስር እንዲፈቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ማክሰኞ የካቲት 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ትዕዛዝ ሰጠ፡፡

የሥር ፍርድ ቤትን ትዕዛዝ በመቃወም የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ይግባኝ ብሎ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመሄድ፣ በተጠርጣሪው ላይ ቀሪ ምርመራ እንዳለው በማስረዳት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቆ ነበር፡፡ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ግን ይግባኙን ውድቅ ሲያደርግበት፣ ሐሳቡን በመቀየር የክስ መመሥረቻ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱም አሥር ቀናት በመፍቀድ በተሰጠው ቀናት ውስጥ ክስ ማቅረብ ካልቻለ፣ የሥር ፍርድ ቤት ቀደም ብሎ በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ተጠርጣሪውን ከእስር እንዲፈታቸው ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡

ዓቃቤ ሕግ በይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት በተሰጠው አሥር ቀናት ውስጥ ክሱን መመሥረት ባይችልም፣ የሥር ፍርድ ቤት የክስ መመሥረቻ 15 ቀናት እንዲፈቅድለት አቅርቦ ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ የተጠርጣሪ ጠበቆች አስተያየት እንዲሰጡበት ሲጠይቅ፣ የሥር ፍርድ ቤት የበላይ ፍርድ ቤትን ትዕዛዝ መፈጸም እንጂ ያንን አልፎ የሚያከራክርበት ሥልጣን እንደሌለው በመግለጽ፣ ደንበኛቸው በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መሠረት ከእስር እንዲፈቱላቸው ጠይቀው ነበር፡፡

ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 109(1) መሠረት ክስ የመመሥረቻ ጊዜና ቀናት ብቻ መሆኑን ቢደነገግም፣ በተለያዩ አዋጆች ተጨማሪ ጊዜ ማስፈቀድ የሚቻል መሆኑን ለማስረዳት ሞክሮ ነበር፡፡

ፍርድ ቤቱ ግን የሁለቱንም ወገኖች መከራከሪያ ሐሳብ በማለፍ፣ ቀደም ብሎ ከሰጠው ትዕዛዝ ውጪ ተጨማሪ ትዕዛዝ የመስጠት ሥልጣን እንደሌለው በመግለጽ፣ ተጠርጣሪው በሌላ ፍርድ ቤት አመልክተው ከእስር እንዲፈቱ ማድረግ እንደሚችሉ (HabeasCorpus) በመግለጽ መዝገቡን ዘግቶት ነበር፡፡

የተጠርጣሪው ጠበቆች በድጋሚ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ በማለት፣ ቀደም ብሎ የሰጠው ትዕዛዝ ተግባራዊ አለመሆኑንና የሥር ፍርድ ቤት መዝገቡን እንደዘጋው በመግለጽ አመልክተዋል፡፡ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የሥር ፍርድ ቤት ለዓቃቤ ሕግ የተፈቀደለት አሥር ቀናት ሲጠናቀቅ ተጠርጣሪን እንዲፈታ ትዕዛዝ መስጠቱን አስታውሶ፣ ግለሰቡ አቤቱታው እስካቀረበበት ቀን ድረስ (ከየካቲት 1 እስከ 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ) ለሕገወጥ እስር መዳረግ እንዳልነበረባቸው በመግለጽ፣ ከእስር እንዲፈቱ በድጋሚ ትዕዛዝ መስጠቱ ታውቋል፡፡ 

ምንጭ፦ ረፖርተር
@tsegabwolde @tikvahethiopia