አ.ሳ.ቴ.ዩ‼️

#የአዳማ_ሳይንስና_ቴክኖሎጂ_ዩኒቨርሲቲ ከጥር 12 እስከ 14 ቀን 2011ዓ.ም. ሁሉም የመደበኛ ቅድመ ምረቃ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲውን ለቀው እንዲወጡ መወሰኑን ተከትሎ፣ ተማሪዎቹና የዪኒቨርሲቲው አስተዳደር እየተወዛገቡ ነው። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት #ለሚ_ጉታ (ዶ/ር)የተላለፈው ውሳኔ ትክክል ነው ሲሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ተማሪዎቹ ግቢውን ለቀው እንዲወጡ የተወሰነው ውሳኔ ሕጉን መሠረት ያደረገ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ያስረዱ ቢሆንም፣ ተማሪዎቹ የተወሰደው ዕርምጃ መሬት ላይ ያለውን #እውነታ ከግምት ያላስገባ ነው በማለት #ተቃውመውታል።

ዩኒቨርሲቲው ከጥር 15 ቀን ጀምሮ ለቅድመ ምረቃ ተማሪዎች የሚሰጠውን ማንኛውንም አገልግሎት እንደሚያቋርጥ ጥር 12:በዩኒቨርሲቲው ሰሌዳ ባወጣው ማስታወቂያ ይፋ አድርጓል፡፡

በዩኒቨርሲቲው ሴኔት መመሪያ መሠረት አንድ ተማሪ በሴሚስተር መከታተል ያለበት ቢያንስ ሰማንያ በመቶ የትምህርት ክፍለ ጊዜ ሲሆን፣ ተማሪዎቹ በሴሚስተሩ ከተቀመጠው የትምህርት ክፍለ ጊዜ 34.4 በመቶ እንዳልተከታተሉ፣ በመመሪያው አንቀጽ 101.2 እና 231.3መሠረት በዩኒቨርሲቲው ሴኔት ውሳኔ ዕርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ሆኖ በማግኘቱ ዕርምጃው መወሰዱን በዩኒቨርሲቲው የማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ ይፋ የሆነው ማስታወቂያ ይገልጻል፡፡

ይህን ያህል የትምህርት ክፍለ ጊዜ ሊከታተሉ ያልቻሉት በተደጋጋሚ ለተቃውሞ ሠልፎች በመውጣታቸው እንደነበር ተማሪዎቹ ገልጸው፣ ከወር በፊት በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ውስጥ ሦስት ተማሪዎች ሕይወት ማለፉ ለተቃውሞዎቹ መራዘም ምክንያት መሆኑንም አክለዋል፡፡ በዚህ ክስተት ማግሥት ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች የአጋማሽ ፈተና እንዲወስዱ ማስታወቂያ ወጥቶ እንደነበር፣ ፈተናውን መውሰድ እንደማይችሉ ቢገልጹም ሰሚ አለማግኘታቸውን ተማሪዎቹ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ለተከታታይ ዘጠኝ ቀናት የመማር ማስተማር ሒደቱ ተቋርጧል በማለት የተላለፈውን ውሳኔ ተቃውመዋል፡፡

‹‹ይኼንን ፈተና መውሰድ ያልቻልነው በሦስቱ #ወንድሞቻችን ላይ የደረሰው ድንገተኛ ሞት ምክንያት በደረሰብን መሪር #ሐዘንና #ድንጋጤ እንዲሁም ሥርዓተ ቀብር ለመፈፀም ወደ የትውልድ ቦታቸው (አሰላ፣ አለታ ወንዶና ባህር ዳር) በመጓዛችን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ተገቢውን ዝግጅት አላደረግንም፤›› ሲሉ ፈተናው እንዲራዝም የጠየቁበትን ምክንያት ለሪፖርተር ያስረዱ ሲሆን ‹‹ዋናው ጥያቄያችንም የደኅንነት ጥያቄ ነው›› ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የሞቱትን ተማሪዎች በሚመለከት ከአዳማ ፖሊስ መምሪያና ከቅዱስ ጳውሎስ ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የአስክሬን ምርመራ ውጤት እንደደረሳቸው ወዲያውኑ ለተማሪዎች ይፋ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱም ይህ ሁኔታ ከመፈጠሩ በፊት ተማሪዎቹ የሁለተኛና የሦስተኛ ዲግሪ ዕድል ይመቻችልን እንዲሁም የሥራ ዕድል ትስስር ከኢንዱስትሪዎች ጋር እንደሚፈጠርልን ቃል ተገብቶልን ነበር በሚል ከሦስት ሳምንት በላይ ትምህርት አቋርጠው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ እነዚህ ቀናት ሁሉ ባክነው የመጀመሪያውን መንፈቀ ዓመት ዕቅድ ማሳካት ስለማይቻል እንደ አዲስ የመማር ማስተማሩ ሒደት የካቲት 25 እና 26 ቀን 2011 ዓ.ም. እንዲጀመር በሴኔቱ ተወስኗል ብለዋል፡፡ የባከነውን የትምህርት ክፍለ ጊዜ ለማካካስም አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መልሰን ለመጥራት ርብርብ እያደረግን እንገኛለን ሲሉም አክለዋል፡፡

ምንጭ፦ ሪፖርተር
@tsegabwolde @tikvahethiopia