ተጨማሪ ባንኮች ተዘረፉ‼️

በኦሮሚያ ክልል ወለጋ አካባቢ ተጨማሪ ስድስት ባንኮች በታጣቂዎች በትላንትናው ዕለት መዘረፋቸውን አንድ የአካባቢው ባለስልጣን ለDW ገለጹ። ባለፉት ሁለት ቀናት ብቻ በሁለት የወለጋ ዞኖች የተዘረፉት ባንኮች 17 መድረሱን የየአካባቢው ባለስልጣናት ገልጸዋል።

የቄለም ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ታመነ ኃይሉ ዛሬ ለDW እንደተናገሩት በአካባቢያቸው ባሉ ስድስት የመንግስት እና የግል ባንኮች ዝርፊያው የተፈጸመው ትላንት እሁድ ከቀኑ አምስት ሰዓት ጀምሮ ነው። “በትላንትናው ዕለት የባንክ ዘረፋ የተካሄደው በሃዋ ገላን ወረዳ፣ እሮብ ገበያ ላይ፣ በአንድ የንግድ ባንክ እና የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ [ላይ] ነው። እዚያው ወረዳ ላይ መቻራ የምትባል ከተማ ላይ አንድ የንግድ ባንክ እና የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ ተዘርፈዋል። ከዚያ ደግሞ ሰዲ ጨንቃ ወረዳ ላይ በጨንቃ ከተማ አንድ የንግድ ባንክ፣ አንድ የኦሮሚያ የህብረት ስራ ባንክ ዝርፊያ ተካሂዶበታል” ብለዋል።

ተዘረፉ በተባሉት ባንኮች እስካሁን መጠኑ ያልታወቀ ገንዘብ በታጣቂዎች መወሰዱን የገለጹት የቄለም ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ የየባንኮቹ ሰራተኞች በታጣቂዎች ታግተው ተወስደዋል የሚል ስጋት እንዳለም አስረድተዋል። “ ካሸሪዎች [ገንዘብ ያዥዎች] እና ስራ አስኪያጆችን ይዘው ሄደዋል ነው የሚባለው። እንግዲህ ሰዎቹን ስላላገኘን እስካሁን ምን ያህል ገንዘብ ተወሰደ የሚለውን ማወቅ አልቻልንም። ግን ደግሞ ሰዎቹን ይዘው ሄደዋል የሚል መረጃ ነው ያለን” ሲሉ አብራርተዋል።

ታጣቂዎቹ ከባንክ ዘረፋ በተጨማሪ በሁለት ወረዳዎች ያሉ የመንግስት መስሪያ ቤት ማውደማቸውን አቶ ታመነ ይናገራሉ። “በላሎ ክሌ የመንግስት መስሪያ ቤት አቃጥለዋል። በዋሃ ገላን፣ በየ ማለጊ ወረዳ ላይም የመንግስት መስሪያ ቤት የተቃጠለበት ሁኔታ ነው ያለው። እንግዲህ እነኚህ ወረዳዎች ሰራዊት የሌለበት ወረዳ ነው። ሰራዊት ከሌላ አጎራባች ቦታ እስኪደርስ ይሄን ጉዳት አድርሰው የታጠቁት ኃይሎች ከአካባቢው ተንቀሳቅሰዋል” ብለዋል።

ዘረፋ እና የንብረት ቃጠሎ በደረሳባቸው ቦታው ግጭት እንደሌለ የቄለም ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ ተናግረዋል። አሁን በቦታዎቹ ላይ የጸጥታ ኃይሎች ገብተው ህዝቡን እየያረጋጉ እንደሚገኙም ገልጸዋል። በአካባቢው የመከላከያ ሰራዊት በሄሊኮፕተር ታግዞ ጥቃት ፈጽሟል የሚባለውንም #አስተባብለዋል።

Via DW
@tsegabwolde @tikvahethiopia