የዓመታት የቤት ጥያቄ ...

" ለልማት ተነሽዎች ለምን ቤት ተሰጣቸው አንልም ፤ ለረዥም ዓመታት ፍትሐዊነት በጎደለው መንገድ ለእኛ ሳይሰጥ መቅረቱ አሳዝኖናል " - ቅሬታ አቅራቢዎች

ለ21 ዓመታት ኮንዶሚኒየም ይደርሰናል ብለው ሲቆጥቡ የቆዩ የኮንዶሚኒየም ነባር ተመዝጋቢዎች ዕጣ ሳይወጣላቸው፣ ቤቶቹ ለልማት ተነሽዎች በመሰጠታቸው ቅሬታ አቀረቡ፡፡

ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ የኮንዶሚኒየም ቤቶችን በዕጣ ለማግኘት ሲጠባበቁ የቆዩ በርካታ ተመዝጋቢዎች እያሉ፣ ለልማት ተነሽዎች ቤቶች መሰጠታቸው ኢፍትሐዊ እንደሆነ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ገልጸዋል፡፡

ይህን ቅሬታ ያቀረቡት ለሪፖርተር ጋዜጣ በሰጡት ቃል ነው።

" ለልማት ተነሽዎች ለምን ቤት ተሰጣቸው አንልም " ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎች " ለረዥም ዓመታት ፍትሐዊነት በጎደለው መንገድ ለእኛ ሳይሰጠን መቅረቱ አሳዝኖናል " ብለዋል።

ለልማት ተብሎ ቤታቸው የፈረሰባው ዜጎች ቤት ሲሰጣቸው የ1997 እና የ2005 ዓ.ም. የኮንዶሚኒየም ቤቶች ተመዝጋቢዎች ጉዳይ በዝምታ መታለፉ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል፡፡

የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ እስኪያልቅ ድረስ ለምን በመንግሥት የተሠሩ ቤቶች አይሰጡንም ? ያሉት ተመዝጋቢዎቹ፣ ለሁለት አሠርት ዓመታት ቤት ለማግኘት በመጠበቃቸው በተለየ ሁኔታ በከተማ አስተዳደሩ ሊስተናገዱ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ የቤት ኪራይና የልጆች ትምህርት ቤት ክፍያዎች ጣራ በመንካታቸው፣ ለችግር ተዳርገናል ያሉት ተመዝጋቢዎች፣ የኢትዮጵያ ዜጋ አይደለንም ወይ ሲሉም ቅሬታቸውን  አሰምተዋል፡፡

ለዓመታት ምላሽ በተነፈገው ጥያቄያቸው ምክንያት በመንግሥት ላይ ያላቸው እምነት መሟጠጡን ገልጸዋል፡፡

ተመዝጋቢዎቹ ለሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም፣ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና ሌሎች ተቋማት ቅሬታቸውን ቢያሰሙም እስካሁን መፍትሔ እንዳላገኙ አክለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ታምራት ምን ምላሽ ሰጡ ?

- አጠቃላይ የቤቶች ግንባታ ከሁለትና ከሦስት ዓመት ተኩል በኋላ የብድር አቅርቦት ችግር ተጨማሪ ግንባታ ማድረግ አላስቻለም፡፡

- ችግሩ እስኪፈታ ድረስ ግንባታ አይካሄድም ፤ ኮርፖሬሽኑ ያለበትን ውዝፍ ዕዳ እስኪከፈል ድረስም ሲያገኝ የነበረው ብድር ተከልክሏል።

- ኮርፖሬሽኑ ካለበት ዕዳ ውስጥ 36 ቢሊዮን ብር ተመላሽ አድርጓል ፤ ቀሪ 37.7 ቢሊዮን ብር ያልተከፈለ ውዝፍ ዕዳ አለበት ፤ ለመክፈልም የተለያዩ አማራጮችን እያጤንን ነው።

- በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብድር የሚሰጠው ለማጠናቀቂያ ሥራ ብቻ ነው። ለሰፊ የቤት ግንባታ ግን ተጨማሪ ብድር አይሰጥም።

-  ለልማት ተነሽዎች ቅድሚያ መስጠትን መመርያው የሚያዝና የሚደግፈው ነው። ነገር ግን የኮንዶሚኒየም ዕጣ ጠባቂዎችን ወደ ጎን ከመግፋት ጋር መገናኘት የለበትም።

- የቤት አቅርቦት ጉዳይ የ1997 እና የ2005 ዓ.ም. የቤት ተመዝጋቢዎች ችግር ብቻ ሳይሆን፣ በአጠቃላይ በቤት አቅርቦቱ በአማራጭ የቤት ልማት ላይ እየተሠሩ ነው።

- ከተለመዱት 40/60 እና 20/80 ቤቶች በተጨማሪ በ70/30 ፕሮግራምና በማኅበር ቤቶች አቅም ያላቸው እንዲገነቡ የሚያስችል አሠራር ተዘርግቷል።

- ኮርፖሬሽኑ እስካሁን የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ሲገነባ የነበረው በቦንድ ግዥ ነበር፤ አሁን ግን የከተማ አስተዳደሩ ካለው በጀት ላይ እየመደበ ብድሩን እየከፈለና ለኪራይ የሚሆኑ ቤቶች እየገነባ ነው።

- ከዚህ በተጨማሪ መንግሥትና ባለሀብቶች ተቀናጅተው የሚገነቧቸው ቤቶች አሉ ፤ ለዝቅተኛ የኅብረተሰብ ክፍሎች እየተሰጡ ነው።

- የኮንዶሚኒየም ተመዝጋቢዎችን በተመለከተ ቁጠባ ያቋረጡ አሉ። ነገር ግን አሁንም ኮንዶሚኒየም ተመዝጋቢዎች የሉም ወይም ጨርሰን ሰጥተናል አላልንም።

- የኮንዶሚኒየም ተመዝጋቢዎች ቅሬታ ትክክል ነው። ነገር ግን ከተማው ያለበትን የቤት አቅርቦት ችግር ሲፈታ የተመዝጋቢዎቹን ችግርም በዚያው ይፈታል።

- የነባሩ የዕጣ አወጣጥ ሒደት ቆሟል ወይም አልቆመም ብለን መናገር አንችልም፤ ምናልባት የባንክ ብድር ከተመለሰ እንደገና በሌላ ብድር ቤቶች ተገንብተው ለዕጣ ጠባቂዎች ለመስጠት ጥረት ይደረጋል።

- የተመዝጋቢዎች ዕጣ የማውጣት ሒደት ይቀጥላል ወይም አይቀጥልም የሚለው በቤት አቅርቦት ሁኔታው ይወሰናል።

- ከኮሪደር ልማት ተነሺዎች በአንድም በሌላም መንገድ ቢጣራ ተመዝጋቢዎች አሉ፡፡ ለኮሪደር ልማት ተነሽዎች የ40/60 እና የ20/80 ቤቶች ተሰጥተው አልቀው ወደ ኪራይ ቤት እየተገባ ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የሕግና የአስተዳደር በደል ምርመራ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መንግሥቱ ቀና በበኩላቸው፣ በ1997 ዓ.ም. ኮንዶሚኒየም ለማግኘት ተመዝግበው ዕጣ ያልወጣላቸውን በተመለከተ ኮርፖሬሽኑ በደብዳቤ መጠየቁን ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብም ምላሽ አለመገኘቱን አቶ መንግሥቱ ገልጸው፣ እንደገና በደብዳቤ ተጠይቆም ምላሽ ካልተገኘ ወደ  የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለማምራት መታቀዱን ተናግረዋል። #ሪፖርተርጋዜጣ

@tikvahethiopia